ህግ የማስከበሩ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ህግ በመጣስ የሙያ ስራ በሰሩ አንድ መቶ ሰላሳ አምስት የሂሳብ እና ኦዲት ባለሙያዎች እንዲሁም አምስት በወንጀል ተግባር በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱን አሳወቀ፡፡

እርምጃ የተወሰደባቸውም በ2013 በጀት ዓመት የቦርዱ የመጀመሪያዉ ግማሽ ዓመት አፈፃፀም በህግ አገልግሎት እና ህግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት በኩል ከቦርዱ የሂሳብና ኦዲት ሙያ ፈቃድ ወስደዉ በወቅቱ ሳያሳድሱ አገልግሎት የሰጡ አንድ መቶ ሰላሳ አምስት የሂሳብ እና የኦዲት ባለሙያዎች እና ድርጅቶች ላይ መሆኑን የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ገልፀዋል፡፡

ዳይሬክተሩ በማከልም እዉቅና ካላቸዉ ባለሙያዎች ባሻገር በሚመለከታቸው የኦዲት ድርጅቶች ያልተመረመሩ የሂሳብ መግለጫዎችን የኦዲት ምርመራ የተደረገባቸው በማስመሰል እንዲሁም የተጭበረበረ ፊርማ እና ማህተም በማሳረፍ በወንጀል የጠረጠራቸውን እዉቅና ያልተሰጣቸዉ አምስት ግለሰቦች በምርመራ ለማረጋገጥ ለፍትህ አካላት ማስተላለፉን አስረድተዋል፡፡

በሂሳብ መግለጫዎች ላይ የሚከናወኑ ማጭበርበሮች በባለሙያዎች ክትትል እና በማህበረሰቡ ቀጥተኛ ጥቆማ እንዲሁም በምርመራ ስራዎች የሚደረስባቸው መሆኑ እንዳለ ሆኖ ሪፖርት አቅራቢ አካላትም ለፋይናንስ ስርዓቱ ጤናማነት ህጋዊ እና የዜግነት ግዴታቸውን በጥንቃቄ መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡