ለሒሳብ ሙያ ጥራት መሻሻል የባለሙያዎቹ ሚና ወሳኝ ነው

የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ በሂሳብ/ኦዲት ባለሙያዎች ፍቃድ አሰጣጥ እና የሒሳብ ሙያ ማህበራት ምዝገባ መመሪያ ቁጥር ኢ.ሂ.ኦ.ቦ. 805/2013 ከአዳማ ከተማ እና አካባቢዋ የሒሳብ እና ኦዲት ባለሙያዎች ጋር ኅዳር 02 ቀን 2014 ዓ.ም. እንዲሁም የሪፖርት አቅራቢ አካላት መለያ መስፈርት እና ምዝገባ መመሪያ ቁጥር ኢሂኦቦ 804/2013 ላይ ኅዳር 03 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ኤክስኪዩቲቭ ሆቴል የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት አካሄደ፡፡

በዕለቱም የቦርዱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር እንደተናገሩት “ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ የሂሳብ ሙያ አገልግሎት አሰጣጥ እና የቁጥጥር ሥርዓት አለመዳበር በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳረፈ መሆኑን ገልፀው የመመሪያዎቹ መውጣት ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ባለሙያዎችን በማፍራት እና ጥራት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት በማቅረብ ከፍተኛ የህዝብ ጥቅም ያለባቸውን የልማት ተቋማት እና ሌሎችንም ሪፖርት አቅራቢ አካላት ውጤታማ ለማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ጠንካራ የሂሳብ ሙያ ሥርዓት መኖር የፋይናንስ ሥርዓቱ ጤናማነት በህጋዊ የሂሳብ መግለጫ ስለሚደገፍ ባለሀብቶች፣ አበዳሪዎች እና ሌሎችም የፋይናንስ ሪፖርቶቹ ተጠቃሚዎች የሚወስኗቸው ውሳኔዎች በእውቀት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አስተማማኝነቱ የላቀ ነው” ብለዋል፡፡

የቦርዱ የህግ አገልግሎት እና ህግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወርቁ አዲስ በሁለቱም ቀናት በመመሪያዎቹ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ በመስጠት ለውያይት ያቀረቡ ሲሆን በተለይ ከቦርዱ ፍቃድ ሳይሰጣቸው የሙያ ሥራ ላይ በተሰማሩ አካላት ላይ ቁጥጥር አለመደረግ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው የቅንጅት ሥራ አለመጠናከር፣ የቦርዱ ለሪፖርት አቅራቢ አካላት ምዝገባ ተደራሽ አለመሆንን የተመለከቱ እና ሌሎችም ሃሳቦች በተሳታፊዎች ተነስተው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በመጨረሻም በገቢዎች ሚኒስቴር የአዳማ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ስመኝ ንጉሤ ለዓለም ሥልጣኔ በርካታ አስተዋፅዖ ያበረከተች ሀገራችን ለውጦችን ለመቀበል ተግዳሮቶች እንደሚበዙባት አውስተው የደረጃዎቹ ትግበራ በእውነተኛ መረጃ ላይ ከተመሰረተ የሂሳብ መግለጫ ሀገር መሰብሰብ ያለባትን ገቢ በመሰብሰብ ለተገቢው የህዝብ አገልግሎት ለማዋል እና ፍትሐዊነትን ለማንገሥ ትልቅ መሳሪያ መሆኑን በመጥቀስ ለተግባራዊነቱ በጋራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡