ለመንግስት የልማት ድርጅቶች IFRS ስልጠና ተሰጠ፡፡

************************************************

የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ከየካቲት 28-30/2015 ዓ.ም. የሚቆይ የIFRS ትግበራ የግንዛቤ ማስጨበጫ በዲ-ሌኦፖል ሆቴል ለመንግስት የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡

 

የግንዛቤ ማስጨበጫው ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች ትግበራን አስመልክቶ ሪፖርት አቅራቢ አካላት ዓመታዊ የሂሳብ መግለጫቸውን በIFRS መሠረት አዘጋጅተው ወደ ቦርዱ እንዲያቀርቡ ለማስቻል ሲሆን በሥልጠናው ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታ እና አስተዳደር፣ ለኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ለፋይናንስ ቢሮ ተጠሪ የሆኑ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሳታፊ ናቸው፡፡

 

በመድረኩም የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የIFRS ትግበራ መነቃቃትን እያሳየ መሆኑን ጠቅሰው በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች በደረጃዎቹ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት ማስፈለጉን በማስታወስ ግንዛቤ ማስጨበጫውም ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በዘርፉ አቅም ባላቸው ባለሙያዎች የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው ተሳታፊዎች ለስራቸው ውጤታማነት የተሻለ ግንዛቤ እንደሚጨብጡም ተናግረዋል፡፡

 

በመድረኩም የIFRS ፅንሰ ሃሳብን ጨምሮ በትግበራ ወቅት ያጋጠሙ እና ሊያጋጥሙ የሚችሉ የተለያዩ ተግዳሮቶችን መሰረት ያደረጉ ተጨባጭ ምሳሌዎችን በማንሳት በተሳታፊዎች የቡድን ውይይት ተካሂዷል፡፡