ለሪፖርት አቅራቢ አካላት በሙሉ

ጉዳዩ፡ የሪፖርት ማቅረቢያ ጊዜ እና የሪፖርት አቅራቢዎች መለያ መስፈርት ስለመሻሻሉ

መንግስት ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ሥርዓት በመዘርጋት የተመቸ የንግድ አና የኢንቨስትመንት ከባቢ በመፍጠር ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የሚኖረውን ከፍተኛ ጠቀሜታ፣ እንዱሁም የተጠናከረ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ሙያ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለመደገፍ፣ ለማበረታታት እና ለማረጋጋት የሚጫወተውን ቁልፍ  ሚና በመገንዘብ በሀገር ውስጥ በሚገኙ በግል እና በመንግስት ዘርፍ ባሉ ድርጅቶች ላይ ተፈፃሚ የሚሆን የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘዉ  አዋጅ  ቁጥር 847/2006ን እና አዋጁንም ለማስፈፀም “የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ” ማቋቋሚያ ሥልጣን እና ተግባሩን መወሰኛ የሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁጥር 332/2007ን አውጥቷል።

በአዋጁ አንቀፅ 5/1 ላይ ተፈጻሚነት የሚኖራቸዉ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች በማለት ዓለም አቀፉ የሂሳብ አያያዝ ደረጃዎች ቦርድ ያወጣቸዉን፡

ሀ/ ዓለም አቀፍ  የፋይናንስ  ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ደረጃዎች፣

ለ/ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች ለአነስተኛ እና መካከለኛ ድርጅቶች እና

ሐ/ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት ዓለምአቀፍ የፐብሊክ ሴክተር የፋይናንስ  ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎችን እንዲተገብሩ ተደንግጓል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 4/2/መ/ ቦርዱ ሪፖርት አቅራቢ አካላትን የህዝብ ጥቅም ያለባቸዉ አካላት ወይም አነስተኛ እና መካከለኛ ድርጅቶች ብሎ መለየት የሚያስችል መስፈርት እንደሚያወጣ እና በአዋጁ አንቀጽ 8/1 ማንኛዉም ሪፖርት አቅራቢ አካል ቦርዱ በሚያወጣዉ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሪፖርቱን ለቦርዱ ማቅረብ አንዳለበት ተደንግጓል።

በዚሁ መሰረት ቦርዱ የአምሰት ዓመት ስተራቴጂክ እቅድ ላይ የትግበራ ጊዜ እና የሪፖርት አቅራቢ አካላት መለያ መሰፈርት አዘጋጅቶ የደረጃዎቹን ትግበራ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።

ሆኖም ግን በቦርዱ እና በሪፖርት አቅራቢዎች በተከሰቱ ዉስጣዊ እና ዉጫዊ  ምክንያቶች አፈፃፀሙ ዝቅተኛ ሆኖ በመገኘቱ ቦርዱ የሪፖርት ማቅረቢያ ጊዜዉን እና የመለያ መስፈርቶቹን እንደሚከተለዉ አሻሽሏል።

ይህ ማሻሻያ የሚያገለግለዉ አስከ አሁን የትግበራ ሥራ ላልጀመሩ ሪፖርት አቅራቢዎች ሲሆን ያለፈውን የትግበራ ጊዜ ጠብቀው ሪፖርታቸዉን ለቦርዱ ያቀረቡትን ወይም ለማቅረብ በሂደት ላይ ያሉትን በዚህ አጋጣሚ እያመሰገንን የተሻሻለዉ የትግበራ ጊዜ የማይመለከታቸዉ መሆኑን እየገለጽን የሪፖርት ማቅረቢያ ጊዜውና የመጠን መለያ መስፈርቶቹ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

 1. የሪፖርት ማቅረቢያ ጊዜ
  • እስከ 2015 ./ .. 2023/ ሙሉ ደረጃዎችን /full IFRS/ የሚተገብሩ፡
   • ከፍተኛ የህዝብ ጥቅም ያለባቸዉ (Significant PIEs)፣
   • ሌሎች የህዝብ ጥቅም ያለባቸዉ (Other PIEs) ሲሆኑ፣
  • አስከ 2016 . /.. 2024/
   • አነስተኛ እና መካከለኛ ድርጅቶች /IFRS for SMEs/ ደረጃዎችን እና
   • የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት /IPSASs/ የሚተገብሩ ሆኖ በተ.ቁ.1.1.1. የተጠቀሰው ከፍተኛ የህዝብ ጥቅም ያለባቸው

ሀ. የሚያወጡትን የግዴታ የምስክር ወረቀት /Debt or equity/ ቍጥጥር በሚደረግበት ሥርዓት ዉስጥ ለግብይት ያዋለ/ለማዋል በዝግጅት ላይ ያለ ማንኛዉም ኩባንያ፣

ለ. ባንኮች፣ ኢንሹራንሶች እና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት፣

ሐ. በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ የልማት ድርጅቶች፣

መ. የአክሲዮን ኩባንያዎች፣

ሠ. በሚመለከተዉ የመንግስት አካል ቁጥጥር የሚደረግበት የጡረታ፡ የፕሮቪደንት ፈንድ እና ተመሳሳይ ተቋም፣

ረ. የህብረት ሥራ ዩኒየኖች፣

ሰ. ቁጥጥር የሚደረግባቸዉ የሸማቾች ማህበራት፣

ሸ. በሚመለከተዉ አካል ቁጥጥር የሚደረግባቸዉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት፣ እና

ቀ. የኢትዮዽያ የምርት ገበያ አባላት ናቸው፡፡

 

 1. የመጠን መለያ መስፈርት
  • ሌሎች የህዝብ ጥቅም ያለባቸዉ ድርጅቶች
   • ዓመታዊ ሽያጭ፡- 300 ሚሊዮን ብር እና ከዚያ በላይ፣
   • ጠቅላላ ሀብት/ንብረት፡- 200 ሚሊዮን ብር እና ከዚያ በላይ፣
   • ጠቅላላ ዕዳ፡- 200 ሚሊዮን ብር እና ከዚያ በላይ፣ እንዲሁም
   • የሠራተኛ ቍጥር፡- 200 እና ከዚያ በላይ ያላቸው እና ከአራቱ መስፈርቶች ሁለቱን የሚያሟሉ ሙሉ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን /full IFRSs/ ይተገብራሉ።
  • አነስተኛ እና መካከለኛ ድርጅቶች
   • ዓመታዊ ገቢ/ሽያጭ፡- ከ20ሚሊዮን ብር እስከ 300ሚሊዮን ብር፣
   • ጠቅላላ ሀብት/ንብረት፡- ከ20 ሚሊዮን ብር እስከ 200 ሚሊዮን ብር፣
   • ጠቅላላ ዕዳ፡– ከ20 ሚሊዮን ብር እስከ 200 ሚሊዮን ብር እና
   • የሠራተኛ ቁጥር፡- ከ20-200 ሠራተኛ ያላቸው ሆኖ ከአራቱ ሁለቱን መስፈርቶች የሚያሟሉ ለአነስተኛ እና መካከለኛ ድርጀቶች የሚያገለግለዉን /IFRS for SMEs/ ይከተላሉ።

ሀ. ማንኛውም ኩባንያ በተ.ቁ 2.1 ላይ ለሌሎች የህዝብ ጥቅም ያለባቸዉ ድርጅቶች የተቀመጡ የመጠን መለያዎችን የማያሟላ ከሆነ፡

ለ. እዳዉን/የአክሲዮን ድርሻዉን ቁጥጥር በሚደረግበት የካፒታል ገበያ ላይ ያላዋለ/ለማዋል በዝግጅት ላይ ያልሆነ፣

ሐ. የብዙ ሰዎችን ሀብት/ንብረት የማስተዳደር ኃላፊነት የሌለበት ከሆነ /IFRS for SMEs/ን የሚተገብር መሆኑን እንገልፃለን፡፡

ከሰላምታ ጋር