ለቦርዱ ዓላማ መሳካት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ወሳኝ ነው

የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ህጎች ላይ ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከአዲስ አበባ ገቢዎች ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎች ጋር ህዳር 9 ቀን 2014 ዓ.ም በኢሊሊ ሆቴል የውይይት መድረክ አካሄደ፡፡

በዕለቱም የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደተናገሩት ጥራት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ደረጃዎች ትግበራ ለጠንካራ ሀገራዊ ኢኮኖሚ እና የህዝቦች ተጠቃሚነት ያለውን ፋይዳ አስረድተው ቦርዱ ለስኬታማነቱ በርካታ ተግባራትን ያከናወነ ቢሆንም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ እና የቅንጅት ስራዎች አስፈላጊነትን አብራርተዋል፡፡

የቦርዱ የህግ አገልግሎት እና ህግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወርቁ አዲስ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ የህግ ማዕቀፎች ላይ እንዲሁም አቶ አሸናፊ ጌታቸው የተሻሻለው የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች ትግበራ ፍኖተ-ካርታ እና ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ስለ ቦርዱ ስልጣንና ተግባር፣ ስለተከለከሉ ተግባራት እና በአለምአቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ስላላቸው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረቦች እንዲሁም የደረጃዎቹ ትግበራ ለግብር አሰባሰብ ያለው አስተዋፅዖ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ በመስጠት ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች ከዋና ዋና ባለድርሻ አካላት አንዱ እንደመሆናቸው መጠን የፋይናንስ ሪፖርት ጥራትን በማስጠበቅ የህዝብን ጥቅም ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት አፈጻፀም ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን የሚቀርቡላቸው ኦዲት የተደረጉ የሂሳብ መግለጫዎች ህጋዊ እውቅና ባላቸው ባለሙያዎች የተዘጋጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ከፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት ጋር በተያያዘ ቦርዱ ያወጣቸው የሪፖርት አቅራቢ አካላት መለያ መስፈርት እና የሚተግብሯቸው ደረጃዎች እንዳለ ሆኖ ከተቀመጡት ደረጃዎች በታች ያሉ ሪፖርት አቅራቢ አካላት ምን መስፈርት መከተል ይኖርባቸዋል? ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ምን የታቀደ ነገር አለ? የሚሉ እና ሌሎችም በርካታ ጥያቄዎች በተሳታፊዎች ተነስተው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡