ለገንዘብ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጠ፡፡

የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ለገንዘብ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ደረጃዎች ትግበራ ሂደትን አስመልክቶ ግንቦት 14 ቀን 2013 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዉይይት ተካሂዷል፡፡

በግንዛቤ ማስጨበጫዉ የቦርዱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸዉን ካስተላለፉ በኋላ ቦርዱ በህግ የተሰጠዉን ኃላፊነት እና ተግባር በመወጣት የሒሳብ እና ኦዲት ሙያ የህዝብን ጥቅም ማስጠበቁን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ሁለንተናዊ ክትትልና ድጋፍ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ደረጃዎች ትግበራ የህግ ማዕቀፎች፣ በኢትዮጵያ የሒሳብ ሙያ ታሪካዊ ዳራ እና አሁናዊ ተጨባጭ ሁኔታ እንዲሁም በደረጃዎች ትግበራ የተከናወኑ ተግባራት እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ላይ ሰፋ ያለ ዉይይት ተካሂዷል፡፡

በተለይ የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ የሒሳብ ስራ ሙያ (Accountancy profession) በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1905 ገደማ ጀምሮ በዘርፉ መነቃቃትን የፈጠረ፣ የዉጪ ተቋማትም ወደ ገበያዉ መቀላቀል የጀመሩ እና በ1940ዎቹ መጀመሪያ ተቆጣጣሪ የመንግስት መስሪያ ቤት መቋቋሙ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የነበረዉ ቢሆንም ከ1974 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገዉ የመንግስት ስርዓት ለዉጥ ምክንያት ሙያዉ መዳከሙን አዉስተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች ትግበራ አዋጅ ቁጥር 847/2006 በተደነገገው መሰረት መፈጸም የሚያስችል አቅም ባለመፈጠሩ ምክንያት የቦርዱ ያለፉት አምስት ዓመታት ክንውን ዝቅተኛ መሆኑን እና ለቀጣይ ክፍተቶችን በመለየት ለተሻለ አፈፃፀም እየተሰራ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡ ደረጃዎቹን መተግበር ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት ቦርዱ ባወጣው መስፈርት መሰረት የሀገሪቱን ህግ አክብረው ትግበራውን ላከናወኑ እና በትግበራ ሂደት ላሉ ሪፖርት አቅራቢ አካላት ምስጋናቸውን ያቀረቡት ወ/ሮ ሂክመት ላልጀመሩት ግን ቦርዱ ባደረገው የማሻሻያ እርምጃዎች መሰረት ከወዲሁ ወደ ትግበራ እንዲገቡ አሳስበው ቦርዱም ቀጣይ የክትትል እና ቁጥጥር ስራዎቹን መፈፀም የሚያስችል አቅም በመገንባት ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የደረጃዎቹ ትግበራ ለሀገራችን የፋይናንስ ስርዓት ጤናማነት ካለዉ ከፍተኛ ጠቀሜታ አንጻር ቦርዱ የተቆጣጣሪነት ሚናዉን በተገቢዉ እንዲወጣ ፣ የባለሙያዎቹን አቅም ለማጎልበት የሚሰራው ኢንስቲቲዩት ምስረታም በፍጥነት መጠናቀቅ እንዳለበት፣የገንዘብ ሚኒስቴርም ኃላፊነቱን እንደሚወጣ እና ግንዛቤ የማስጨበጡ ስራ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡