ማርች 8 ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን ተከበረ

የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ111ኛ ጊዜ “የዛሬ የጾታ እኩልነት ለነገ ዘላቂነት” በሚል እና በሀገራችን ለ46ኛ ጊዜ “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ቃል የተከበረውን “ማርች 8” ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀንን መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም በሊደርሺፕ ኢንስቲትዩት የስብሰባ አዳራሽ አክብሮ ዋለ፡፡

በበዓሉም የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ በበዓሉ የእንኳን አደረሳችሁ የመክፈቻ ንግግራቸው እንደተናገሩት በዓሉ በዚህ ዓመት በሚከበርበት ወቅት ዓለማችን በተለያዩ ሰብዓዊ እና ሁለንተናዊ ቀውሶች እየተናጠች እና ሀገራችንም አንዷ የገፈቱ ቀማሽ መሆኗን ያስታወሱ ሲሆን ለተፈጠሩት ቀውሶች ሴቶች ከሁሉም በላይ የተጋለጡበት ወቅት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለመፍትሔውም በርካታ ርብርቦሽ እየተደረገ ያለ መሆኑን እና የቦርዱ ሰራተኞችም በሀገር ወዳድነት በመደጋገፍ እና ለሰላም በሚደረጉ ሁለገብ ጥረቶች የማይታለፍ ችግር አለመኖሩን በመገንዘብ በባለቤትነት ስሜት እና በቅንጅት በመስራት የመፍትሔ አካል መሆን እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱም የሰው ሃብት ልማትና አስተዳደር ዳ/ት ዳ/ር አቶ ደረሰ መለሰ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሴቶች ቀን በዓል አጀማመር፣ ለበዓሉ ማርች 8 እንዴት እንደተመረጠ እና በሀገራችንም ሆነ በዓለም መድረክ ሴቶች ዕድሉን ካገኙ ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ የበርካቶችን ተሞክሮዎች በማንሳት ለውይይት ያቀረቡ ሲሆን ሰፋ ያለ ውይይትም ተካሂዶበታል፡፡