በመንግስት አስተዳደር አዋጅ እና የዲሲፕሊንና ቅሬታ አፈጻጸም ሥነ ሰርዓት ላይ ስልጠና ተሰጠ

የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ለሰራተኞቹ በመንግስት አስተዳደር አዋጅ ፣የዲሲፕሊንና ቅሬታ አፈጻጸም ሥነ ሰርዓት እንዲሁም የሠራተኛ መነቃቃት/መነሳሳት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና የካቲት 23 እና 24 ቀን 2014 ዓ.ም በአዳማ ከተማ አካሄደ፡፡

የቦርዱ የሰው ሀብት ልማትና አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረሰ መለሰ ባቀረቡት መነሻ ፅሁፍ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ህጎች ከአፄ ሚኒሊክ ዘመነ-መንግስት ጀምሮ የነበረውን ሂደት የዳሰሱ ሲሆን ሲቪል ሰርቪሱ ባለፉት ስርዓቶች በአብዛኛው የተማከለ የአሰራር ስርዓቶችን ይከተል ስለነበር ከበላይ የወረዱ መመሪያዎች እስከታችኛው እርከን ድረስ በተመሳሳይ መልኩ የመፈጸም ዕድል የነበረው መሆኑን ገልጸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጀምሮ ግን ያልተማከለ የአሰራር ሥርዓትን የተከተለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል የቦርዱ የህግ ቡድን መሪ አቶ ደረበ ዳኜ  የሰራተኞች የዲሲፕሊን አፈጻጸምና ቅሬታ አቀራረብ ዙሪያ ባቀረቡት ፅሁፍ የዲሲፕሊን እርምጃ የመውሰድ ስልጣንና ኃላፊነት፣ስለዲሲፕሊን ምርመራ፣ ስለ ዲሲፕሊን እርምጃዎች፣ የዲሲፕሊን ቅጣት አይነቶችና አመዳደብ፣ ከባድ የዲሲፕሊን ቅጣቶችን ስለሚያስከትሉ ጥፋቶች እና በመንግስት ሠራተኞች አስተዳደር ፍርድ ቤት ስለሚታዩ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

 

በመጨረሻም ሠራተኞችን ሊያነቃቁ/ሊያነሳሱ ስለሚያስችሉ ፅንሰ-ሀሳቦች እና አተገባበራቸውን በተመለከተ የቦርዱ የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አልታሰብ አየሁ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በቀረበው ፅሁፍ መነሻነት በሠራተኞች ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዷል፡፡