በማምረቻ ዘርፍ ከተሰማሩ ከፍተኛ ግብር ከፋይ የሪፖርት አቅራቢ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ

የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከማምረቻ/ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ከተሰማሩ ከፍተኛ ግብር ከፋይ ሪፖርት አቅራቢ የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ጋር ከፍተኛ ጥራት ባለው ዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ደረጃዎች ትግበራ ጉዳዮች ላይ ታህሳስ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል የግማሽ ቀን ውይይት አካሄደ፡፡

መድረኩ ከአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በትብበር የተዘጋጀ ሲሆን በመድረኩ ከ50 ኩባንያዎች የተወጣጡ የድርጅት ሥራአስኪያጆች፣ ባለቤቶች እና ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ ለተሰብሳቢዎቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን ባስተላለፉበት ወቅት እንደተናገሩት ሪፖርት አቅራቢ አካላቱ በሀገሪቱ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ሥርኣት ግንባታ ውስጥ ካላቸው ከፍተኛ ሚና አንፃር የሂሳብ መግለጫዎቻቸውን በዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎችን መተግበተር ለተጠቃሚው በሚሰጠው ግልፅ መረጃ የኢንቨስትመንት አቅምን ለማሳደግ እና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዕለቱም የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረጋሳ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግራቸው የንግድ ድርጅቶቹ ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን በማሳደግ ጠንካራ ሀገራዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚናቸውን መወጣት የሚችሉት ደረጃዎቹን ቦርዱ ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት መተግበር ሲችሉ መሆኑን ያብራሩ ሲሆን የቦርዱ የዋና ዳይሬክተር አማካሪ አቶ ወርቁ ዓለሙ በሪፖርት አቅራቢ አካላት መለያ መስፈርት እና የትግበራ ጊዜ ማሻሻያው ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከተሰብሳቢዎችም በርካታ ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን በገበያው ውስጥ አገልግሎቱን መስጠት የሚችሉ የብቁ እና በቂ ባለሙያ እጥረቶችን በተመለከተ፣ የክትትልና ድጋፍ/ስልጠና አሰጣጥ ጉዳዮች፣ ዘርፉን የሥርዓተ-ትምህርቱ አካል ለማድረግ እየተሰሩ ስላሉ ስራዎችና ሌሎችም ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በመጨረሻም የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና የቦርዱ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግራቸው እንደተናገሩት የሀገሪቱን የፋይናንስ ስርዓት በማጠናከር ኢኮኖሚውን ለመገንባት እና የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ደረጃዎቹን መተግበር ቁልፉ ተግባር በመሆኑ ላለፉት አምስት ዓመታት በፍጥነት ወደ ትግበራው በመግባት በርካታ ጠንካራ ተግባራት የተከናወኑ ቢሆንም በተለያዩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች የተጠበቀውን ውጤት ማሳካት አለመቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ መልካም ጅምሮችን በማጠናከርና ክፍተቶችን በመለየት የማሻሻያ ስራዎችን ለመስራት በየደረጃው በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው ሪፖርት አቅራቢ አካላትም ህግን በማክበር እና ህገ-ወጥነትን በመከላከል ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡