በሪፖርት አቅራቢ አካላት፣ የሂሳብ /ኦዲት ባለሙያዎች እና የሙያ ማህበራት ረቂቅ መመሪያ

ላይ በድሬደዋ ከተማ ውይይት ተደረገ

የሪፓርት አቅራቢ አካላት ምዝገባ ፣የሂሳብ ባለሙያዎች ፈቃድ አሰጣጥ እና የሙያ ማህበራት ዕውቅና አሰጣጥ ሪቂቅ መመሪያ ላይ በድሬደዋ ከተማ የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም ከባለድርሻ አካላት ጋር የሙሉ ቀን ውይይት ተደረገ፡፡

የቦርዱ የህግ አገልግሎት እና ህግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወርቁ አዲስ ረቂቅ መመሪያውን ለውይይት ያቀረቡ ሲሆን በውይይቱ ላይ ከከተማ አስተዳደሩ እና ከፌዴራል ከፍተኛ ግብር ከፋይ ሪፓርት አቅራቢ አካላት፣ ከሂሳብ ባለሙያዎች፣ ከክልሉ የተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂዎች ማህበራት፣ ከጅግጅጋ ከተማ የአንበስ ጌታሁን የተመሰከረለት ሂሳብ አዋቂ ድርጀት ባለሙያዎች እና ከሐረር ከተማ የተወጣጡ 44 ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ረቂቅ መመሪያው በተለያዩ ጊዜያት በበቦርዱ ባለሙያዎች እና በሀገሪቱ ከሁሉም ክልል በተወጣጡ የሙያ ማህበራት አመራሮች ጋር ውይይት ሲካሄድበት የነበረ ቢሆንም መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ.ም በጸደቀው የመንግስት አስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ዓ.ም መሰረት ማንኛውም መመሪያው ተፈጻሚ የሚሆንበት አካል በመመሪያው ረቂቅ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ማሳተፍን የሚያስገድድ በመሆኑ ባለድርሻ አካላቱ አስተያየታቸውን እንዲሰጡበት ለውይይት ይፋ መደረጉን አቶ ወርቁ አብራርተዋል፡፡

በዕለቱም በርካታ አስተያየቶችና ጥያቂዎች ተነስተው ውይይት የተካሄደባቸው ከመሆኑ በተጨማሪ ገንቢ ሃሳቦችም ተወስደዋል፡፡

ከተነሱት ሃሳቦች ዋነኞቹ በከተማ አስተዳደሩ የሙያ ፈቃድ ሳይኖራቸው የሂሳብ ስራ የሚሰሩ ግለሰቦች ከመበራከታቸው እና ህጋዊ እርምጃ ካለመወሰዱ የተነሳ በፋይናንስ ስርዓቱ ላይ አደጋ የተጋረጠ ከመሆኑም አልፎ ህጋዊ ዕውቅና ያላቸው ሙያተኞች እንዲዳከሙ እና አንዳንዶቹም ወደ ህግ-ጥሰት እንዲገቡ እየገፋፋ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በመጨረሻም ህጋዊ አሰራርን በመጣስ የህዝብና የሀገርን ጥቅም እየጉዱ ያሉ አካላትን ለመከላከል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ የተጠቀሰ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ የገቢዎች ቢሮ ተወካይ በቅርበት እንደሚከታተሉት አስረድተዋል፡፡