በሪፖርት አቅራቢ አካላት የሂሳብ /ኦዲት ባለሙያዎች እና የሙያ ማህበራት ረቂቅ መመሪያ ውይይት በባህርዳር ከተማ ተከናወነ

የሪፖርት አቅራቢ አካላት ምዝገባ፣የሂሳብ ባለሙያዎች ፈቃድ አሰጣጥ እና የሙያ ማህበራት ዕውቅና አሰጣጥ ሪቂቅ መመሪያ ላይ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም የአንድ ቀን የውይይት መድረክ በባህርዳር ከተማ ተከናወነ፡፡

መድረኩን የአማራ ክልል የሂሳብ አዋቂዎችና ኦዲተሮች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉጌታ አለኽኝ ለተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አሰተላልፈው በረቂቅ መመሪያው ላይ የሁሉም ባለድርሻ አካላት መሳተፍ አስፈላጊነትንም አብራርተዋል፡፡

በዕለቱም ከባህርዳር፣ ከጐንደር፣ ከደሴ እና አካባቢዎቹ የተወጣጡ 45 ባለድርሻ አካላት በውይይቱ ተሳትፈዋል፡፡

ረቂቅ መመሪያውንም የቦርዱ የህግ አገልግሎት እና ህግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወርቁ አዲስ ያቀረቡ ሲሆኑ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጐበት ለግብዓት የሚሆኑ አስተያየቶችም ቀርበዋል፡፡

ከቀረቡ ጥያቄዎችም መካከል እንደ ሀገር በቦርዱ የሚሰጥ የሙያ ፈቃድ እና የክልሎች የሚና መደበላለቅ እስከመቼ መፍትሔ እንደሚያገኝ በተጨማሪም የባለሙያ እጥረትን ለመፍታት የቦርዱ እና የኢንስቲትዩሽን መቋቋም ጉዳዮች አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በተመሳሳይም በተለያዩ ምክንያቶች በክልሉ እየተፈጸሙ ያሉ ህግ ጥሰቶችን ለማስቀረት የክልሉ ዋና ኦዲተር ከማህበሩ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ባለሙያ ተናግረዋል፡፡