በተመረመሩ የፋይናንስ ሪፖርቶች እና በኢብባ ረቂቅ መመሪያ ላይ ውይይት ተካሄደ

የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ በፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች (በIFRS) መሠረት ተዘጋጅተው ከቀረቡለት የሂሳብ መግለጫዎች መካከል ምርመራ ባደረገባቸው እና በብሔራዊ ባንክ “የኦዲት ሙያ ደረጃ መሻሻልን ለማረጋገጥ” በሚል በወጣው ረቂቅ መመሪያ ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ አመራሮች ጋር መጋቢት 7 ቀን 2014 ዓ.ም ውይይት አደረገ፡፡

በውይይቱም የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በፋይናንስ ደረጃዎች(IFRS) መሠረት ተዘጋጅተው እና ኦዲት ተደርገው ከቀረቡለት የሂሳብ መግለጫዎች ውስጥ በአሥራ ሁለቱ ላይ ምርመራ(reveiw) ማድረጉን እና ምርመራ ካደረጋቸው መካከል አንዱ በፋይናንስ ዘርፍ በተሰማሩ ተቋማት መሆኑን የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ አብራርተዋል፡፡

በማብራሪያውም መሠረት በጉልህ የተገኙ የምርመራ ውጤቶችን አቶ አሸናፊ ጌታቸው ለውይይት ያቀረቡ ሲሆን በተለይ ክፍተት በታየባቸው ጉዳዮች ላይ የዕውቀት ሽግግር፣ የአቅም ግንባታ ጉዳዮችና በቅንጅትና በትብብር መሥራት ተቆጣጣሪው አካል (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ) ትኩረት ሊሰጠው የሚገቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በውጤቶቹም ዝርዝር ጉዳዮች እና በየትኛው ዘርፍ (ባንኮች፣የመድን ኩባንያዎች ወይም ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት) የሚለው ባይጠቀስም በቀጣይ ይፋ የሚደረግ መሆኑን ወ/ሮ ሂክመት አብራርተዋል፡፡

በቀጣይም ብሔራዊ ባንክ “የባንኩን ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ የቆየውን የኦዲት ደረጃ ማሻሻሉን ለማረጋገጥ” ብሎ ያዘጋጀውን ረቂቅ መመሪያ በተመለከተ ከህግ ይዘት እና የኦዲት ሙያን ማሻሻል እና ከሙያው ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የማረጋገጥ ሚና በአዋጅ ኃላፊነት የተሰጠው አካል እያለ ተጨባጭ ሁኔታውን ያላገናዘበ መሆኑ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በመጨረሻም የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስተር ደኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ ሁለቱም ተቆጣጣሪ አካላት የፋይናንስ ዘርፉን ደህንነት እና የህዝብን ጥቅም ማስጠበቃቸውን በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ያለ ሚና መቀላቀል ትኩረት ሰጥተው በቅንጅት መስራት በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡