በአገልግሎት አሰጣጥ እና ደንበኛ አያያዝ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ

የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አዲስ ካካሄደው የሠራተኞች ምደባ ጋር በተያያዘ ከጥቅምት 18 እስከ 21 ቀን 2015 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ለቦርዱ ሠራተኞች በአገልግሎት አሰጣጥና ደንበኞች አያያዝ ጉዳዮች ላይ ስልጠና ሰጠ፡፡

ስልጠናው በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ስለሚታዩ ዋናዋና ችግሮች፣ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች፣ ስለ ጊዜ አጠቃቀምና የተግባቦት ክህሎት እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ ፖሊሲ አሰፈላጊነትን ጨምሮ በሌሎችም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያተኮሩ ሰፋ ያለ ግንዛቤን የሚያጎለብት እና ሠራተኞችን ያሳተፈ ነበር፡፡

በስልጠናው ወቅት የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ እንደተናገሩት የስልጠናው ዋና ዓለማ ሰራተኞቹን ስለ ውጤታማ አገልግሎት አሰጣጥ ግንዛቤ ለመስጨበጥ መሆኑን ገልጸው በአገልግሎት አሰጣጥ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮች ከሰራተኛው ወደ ማኔጅመንቱ መምጣት አለባቸው ብለዋል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያ የቦርዱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር ከስልጠናው በኋላ ሁሉም ሰራተኛ በቀጣይ በእጅ ያሉ የሥራ ንብረቶች እና መረጃዎችን በመረካከብ ወደ ተደለደሉደበት የስራ ክፍል መዛወር እና ዕቅዶቻቸውን በመከለስ ወደስራ መግባት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

በስልጠና ራሳችንን በደንብ አይተናል፣ የወሰድነውን ስልጠና ወደ ተግባር ለውጠን ለደንበኞቻችን የተሻለ አገልግሎት በመስጠት የተቋሙን የህዝብ ጥቅም የማስጠበቅ ዓለማ ለማሳካት በተሻለ አቅም፣በተሻለ ሰብዕና እና በተሻለ የአገልጋይነት መንፈስ ወደ ስራ መግባት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ስልጠናው ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በተጋበዙ ምሁራን የተሰጠ ሲሆን በመጨረሻም ተሳታፊ ሠራተኞቹ ከስልጠናው ያገኙት ዕውቀት ለቀጣይ ሥራቸው ከፍተኛ አሰተዋፅኦ ያለው መሆኑንም ገልፀዋል፡፡