ቦርዱ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ቢሮ እና
የቅርንጫፍ ጽ/ቤት አመራሮች ጋር ተወያየ
የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በቅርቡ የሪፖርት አቅራቢ አካላት የመለያ መስፈርት እና የትግበራ ጊዜ ማራዘሚያ ላይ ያደረገውን ማሻሻያ አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ቢሮ እና በሥሩ ካሉ ከአስራ አምስቱም የቅርንጫፍ ጽ/ቤት አመራሮች ጋር የቦርዱ የሥራ ሓላፊዎች በተገኙበት መስከረም 21 ቀን 2012 ዓ.ም. በቢሮው የስብሰባ አዳራሽ የግማሽ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት አካሄደ፡፡
በውይይቱ ላይም የቢሮው ም/ሓላፊ አቶ ዮሴፍ ግርማ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግራቸው ሀገራችን ከገቢ ግብር ከምታገኘው የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አውስተው የገቢ ግብር አሰባበሰብ ደረጃዎች ከፍተኛ ጥራት ባለው የሪፖርት አቀራረብ ሥርዓት፣ በግብር ሰብሳቢው እና በግብር ከፋዩ ማህበረሰብ መካከል ጠንካራ መተማመንን መፍጠር በሚችል አሰራር መደገፍ እንዳለበትና ለሁለቱ ተቋማት የተቀናጀ ስራ የግንዛቤ ማስጨበጫው አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይም የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ እንደተናገሩት መንግስት እያከናወናቸው ካሉ የፋይናንስ ስርዓት ማሻሻያዎች አንዱ በግል፣ በመንግስት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ተፈጻሚ የሚሆኑ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች ትግበራ ተጠቃሽ መሆኑን ጠቅሰው ቦርዱ ተልዕኮውን ለማሳካት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚሰራውን ከቢሮው ጋርም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ የውይይቱ ዓላማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዕለቱም የቦርዱ የሙያ ትምህርት እና ብቃት ማረጋገጫዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወርቁ ዓለሙ የቦርዱን መቋቋም አስፈላጊነት፣ ሥልጣንና ተግባራት እንዲሁም በቅርቡ የተደረገውን የሪፖርት አቅራቢ አካላት መለያ እና የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች ትግበራ ጊዜ ማሻሻያን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያዎቹም ላይ በተሳታፊዎች ሰፋ ያለ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በተለይ አመራሩንና ሙያተኛውን በቂ ግንዛቤ የማስጨበጥ እና በሁለቱ ተቋማት ጠንካራ የቅንጅት ሥራ መሰራት እንዳለበት፣ በህገ-ወጥ ሙያተኞች ላይ ስለሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ፣ የተከናወነው የሪፖርት አቅራቢ አካላት መለያ እና የደረጃዎቹ የትግበራ ጊዜ ማሻሻያ መንስኤዎችና የመሳሰሉት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው በሓላፊዎቹ ገለፃ ተደርጎባቸዋል፡፡
በመጨረሻም የግንዛቤ ማስጨበጫው የአንድ ወቅት ሥራ ሳይሆንና ቀጣይነት እንዲኖረው ቢሮው በሚያቀርባቸው ፍላጎቶች መሰረት ቦርዱ ለመደገፍ ከጎኑ እንደሚሆን፣ በባላድርሻ አካላት መካከል የሚከናወኑ ቅንጅትና ግንኙነቶችን ተቋማዊ የማድረግ ስራ መጠናከር እንደሚገባ እና ለዚህም አስፈላጊው የአቅም ግንባታ በመከናወን ላይ መሆናቸውን የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ አስረድተዋል፡፡