ቦርዱ የ”IFRS” የትግበራ ፍኖተ ካርታን አስመልክቶ ከክልልና ከከተማ አስተዳደሮች ከተጋበዙ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ስራ አስኪያጆች፣ የፋይናንስ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ምክክር አካሄደ

==================================

ነሐሴ 11 ቀን 2015 ዓ.ም

አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የ”IFRS” ትግበራ ፍኖተ ካርታን አስመልክቶ ከክልልና የከተማ አስተዳደሮች ከሚገኙ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ስራ አስኪያጆች፣ የፋይናንስ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር የግማሽ ቀን ምክክር በገንዘብ ሚኒስቴር አዳራሽ አካሄዷል፡፡

የምክክሩ ዓላማ፡- የመንግስት የልማት ድርጅቶች የ”IFRS” ትግበራ ፍኖተ ካርታው ያለበት ደረጃ ምን ላይ እንደሚገኝ በማወቅ ሁሉም የልማት ድርጅቶች ዓመታዊ የሂሳብ መግለጫ ሪፖርታቸውን በስታንዳርዱና በትግበራ ፍኖተ-ካርታው የጊዜ ገደብ መሰረት እንዲተገብሩ ለማስገንዘብ ነው፡፡

በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ የህዝብ ጥቅም ያለባቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች በ”IFRS” አተገባበር ፍኖተ ካርታው መሰረት የፋይናንስ ሪፖርታቸውን በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አተገባበር ደረጃዎች አዘጋጅተው የ2015 በጀት ዓመት በተጠናቀቀ በአራት ወራት ውስጥ ወደ ቦርዱ ገቢ ማድረግ ያለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም ሁሉም የመንግስት የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ ሪፖርታቸውን በስታንዳርዱ መሰረት አዘጋጅተው በተሰጠው የጊዜ ገደብ ማቅረብ ያለበት በመሆኑ፣ በጊዜ ገደቡ በማያቀርቡት ተቋማት ላይ ቦርዱ ወደ ተጠያቂነት ከማምራቱ በፊት በቀሪ ጊዜያት ለማጠናቀቅ ይህ መድረክ መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ በሂደቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ላይ በመወያየት መተግበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በመቀጠል ለምክክሩ የተዘጋጁ ሰነዶች በቅደም ተከተል ገለፃ በባለሙያዎች የተደርጉ ሲሆን፣ በቅድሚያ በቦርዱ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያዎች እና የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃ ዎች /IFRS/ ሥርዓት ትግበራ ዙሪያ የቦርዱ የህግ ማስከበር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ወርቁ አዲስ የሪፖርት አቅራቢ አካላት በትግበራ ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችን በተጨባጭ በማቅረብ በአዋጁ በተቀመጠው ህግና ሥርዓት መሰረት ተደርጎ ስታንዳርዱ ሊተገበር እንደሚገባ ገለፃ አድርገዋል፡፡

በመከተል የህዝብ ጥቅም ያለባቸው ሪፖርት አቅራቢ አካላት ባንኮች፣ ኢንሹራንሶች፣ማይክሮ ፋይናንስ፣ በመንግስት ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሸማቾች እንዲሁም የመንግስት የልማት ድርጅቶች በመሆናቸው በቦርዱ የ”IFRS” ትግበራ ፍኖተ- ካርታው መሰረት በ2015 የሂሳብ መገለጫቸውን ወደ ቦርዱ ማምጣት እንዳለባቸው አስታውሰው፤ እስካሁን ከተለዩት 126 የህዝብ ጥቅም ያለባቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል በስታንዳርዱ መሰረት አዘጋጅተው የሂሳብ መገለጫቸውን ወደ ቦርዱ ያቀረቡ 66ቱ ብቻ በመሆናቸው የበጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ አራት ወራት ውስጥ ቀሪ የመንግስት ልማት ድርጅቶች እንዲያጠናቅቁ የሪፖርት አቅራቢ አካላት ምዝገባና ጥናትና መረጃ አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ለማ እሸቱ ተናግረዋል፡፡

መሪ ስራ አስፈጻሚው አክለውም በቀጣዩ 2016ዓ.ም በሀብት መጠን አነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች በመባል የተለዩ የሪፖርት አቅራቢ አካላት የፋይናንስ ሪፖርታቸውን በ”IFRS for SMEs” ስርዓት በመተግበር የሂሳብ መገለጫቸውን ወደ ቦርዱ የሚያቀርቡ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ቦርዱ ተቆጣጣሪ አካል እንደመሆኑ ከሪፖርት አቅራቢ አካላት የሚቀርቡ ፋይናንሺያል ሪፖርቶች ጥራትን ገምግሞ የማረጋገጥ ተግባር ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በማካሄድ ላይ ሲሆን፤ በግምገማ ግኝቶቹ ላይ የታዩ ችግሮችና ግድፈቶችን በወቅቱ እንዲታረሙ አስተያየት በመስጠት የባለሙያዎችን የሙያ ጥራትን የማስጠበቅ ዓላማ ይዞ እየተገበረ ያለ መሆኑን በዝርዝር ገለፃ ያደረጉት ፋይናንስ ሪፖርት ግምገማ እና የሙያ ጥራት ማረጋገጥ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ አህመድ መሀመድ በያን ሲሆኑ በየጊዜው እየተሻሻሉ የሚወጡትን መስፈርቶች በማካተት ግምገማና ተገቢው አስተያየት የመስጠት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን በማስገንዘብ የሙያ ጥራትን የማረጋገጥ ኃላፊነት የሁላችንም ጥረት መሆኑን አውቀን ዓመታዊ የሂሳብ መግለጫ ሪፖርት በስታንዳርዱ መሰረት ማዘጋጀት እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም በውይይቱ ለተነሱ ሀሳቦች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የቦርዱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ አጎናፍር የ”IFRS” የትግበራ ፍኖተ-ካርታው ከበቂ በላይ ጊዜ ተሰጥቶት ሲተገበር በመቆየቱ አሁን መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል በማየት ቀጣይ አቅጣጫ ለመያዝ ይህ የውይይት መድረክ መዘጋጀቱን በማውሳት የፋይናንስ ሪፖርት አቅራቢ አካላት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት የሂሳብ መግለጫ ሪፖርታቸውን ማቅረብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡