ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ዉይይት ተደረገ፡፡

የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከኢ.ፊ.ዲ.ሪ. የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ህዳር 05 እና 06 ቀን 2013ዓ.ም በቦርዱ ባለፉት አምስት ዓመታት የስትራቴጂክ እቅድ አፈፃፀም እና የቀጣይ አምስት ዓመታት አቅጣጫ ላይ በአዳማ ከተማ ዉይይት አደረገ፡፡

በውይይቱም የቦርዱ ዓላማ ፈፃሚ የስራ ክፍሎች ዳይሬክተሮች እና የስትራቴጂክ እቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ሠራተኞች የተገኙ ሲሆን በዕለቱም የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ ለተሰብሳቢዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

በንግግራቸውም ወጥ የሆነ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ህግ መኖር ያልተማከለ የነበረውን የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ በማማከል ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትንና ተዓማኒነትን በማጎልበት፣ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ለመደገፍ እና የህዝብን ጥቅም ለማስከበር ያለውን ፋይዳ ገልጸው በሀገሪቱ የፋይናንስ የቁቁጥር ስርዓት (regulation) አለመኖር፣ የበቂ እና ብቁ ባለሙያዎች እጥረት እንዳለ ሆኖ ውስብስብ የሆኑ አዳዲስ ደረጃዎችን ኢትዮዽያ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ታደርጋለች ብሎ መደምደሙ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በእለቱም የህግ አገልግሎት እና ህግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወርቁ አዲስ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎችን ለመደንገግ የወጣውን የአዋጅ ቁጥር 847/2006 እና ይህንንም የሚያስተገብር ቦርድ ለማቋቋም የወጣውን ደንብ ቁጥር 332/2007 አስፈላጊነት፣ ዓላማ፣ ራዕይና ተልዕኮ ላይ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

በመቀጠልም የባለፉት አምስት ዓመታት (2008-2012ዓ.ም) አፈፃፀም የተከናወኑና ያልተከናወኑ ተግባራትን፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፣ የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አልታሰብ አየሁ ያቀረቡ ሲሆን የቀጣይ አምስት ዓመታት የትኩረት አቅጣጫን በተመለከተ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

በቀረቡት ማብራሪያዎች ላይ ዉይይት ያደረጉት የቋሚ ኮሚቴ አባላትም ቦርዱ ከተደረገለት ዝቅተኛ ድጋፍና ክትትል  እንዲሁም ከነበሩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶች አንፃር በሂደት አፈፃፀሙን ያሻሻለ መሆኑን ጠቁመዉ ከተጣለበት ኃላፊነትና ተልዕኮዉን ከማሳካት አንፃር በቀጣይ የተቀናጀ የድጋፍ እና ክትትል ስርዓት ሊኖረዉ አንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

  • በተመሳሳይም በየደረጃዉ ያሉ የሚመለከታቸዉ አካላትም በተለይ ዘርፉ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ስርዓት ግንባታ ዉስጥ ካለዉ ወሳኝ ሚና አንፃር ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ፣
  • ለአፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆን የተጠቀሱ ተግዳሮቶች እንዳሉ ሆኖ የሚመለከታቸዉ አካላት የተቀናጀ ትብብር አስፈላጊው እና ስትራቴጂያዊ የሆነ መዋቅራዊ መፍትሔ የሚሻ መሆኑን፣
  • ሙያው የህዝብ ጥቅምን ከማስጠበቅ አንፃር በገባያዉ ዉስጥ ያሉ ሙያተኞች ስነ-ምግባር መቆጣጠር እና ህግ ለማስከበር የሚያስችል የሙያ ስነምግባር ደንብ ሊኖር እንደሚገባ፣ እና
  • ሙያዉን በሃገር አቅፍ ደረጃ ከማሳደግ አንፃር ባለሙያ ለማፍራት እና ለመከታተል የሚያስችል ተቋም ማቋቋም ሂደት፣ የአዋጁንና ደንቦቹን ማሻሻያ በፍጥነት ማከናወን እንደሚገባ፣
  • እንዲሁም የቀጣይ አምስት ዓመት ዕቅድ ቀርቦ ውይይት እንዲደረግ እና የስድስት ወር የአፈፃፀም ሪፖርት መቅረብ እንዳለበት እና ከማን በምን ዓይነት መልኩ ምን እንደሚጠበቅ ተለይቶ መቅረብ ይገባልም ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ቦርዱ ከሚፈለገው ድጋፍና ክትትል እጥረት ውጪ የተጠቀሱት ችግሮች በቦርዱ መፈታት የነበረባቸው እና ለመፍታትም እየተሰራ መሆኑን እንዲሁም እንደተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት የተጠሪነት እና የህግ ማሻሻያዎቹን በቅደም ተከተል ለመፍታት እንደሚሰሩ የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር አብራርተዋል፡፡