ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የህግ፣ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር የትውውቅ ፕሮግራም ተከናወነ

 የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር መጋቢት 17 ቀን 2014 ዓ.ም. የትውውቅ ፕሮግራም አከናወነ፡፡

በትውውቅ ፕሮግራሙ ላይ የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን ባስተለለፉበት ወቅት፤ የሂሳብ ሥራ ሙያ (Accountancy profession) በኢትዮጵያ የነበረውን ታሪካዊ ዳራ፣ ያጋጠሙት ተግዳሮቶች፣ ለቦርዱ መቋቋም መነሻ የሆኑ ምክንያቶች እና ሙያው ያለበትን ሁኔታ አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም የቦርዱ ማቋቋሚያ የህግ ማዕቀፎች፣የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች ዓለም-ዓቀፍ ተሞክሮ እና የኢትዮጵያ ተጨባጭ የትግበራ ሁኔታ እንዲሁም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ በቦርዱ የሥራ ሓላፊዎች ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን ከአባላት ሰፋ ያሉ ሓሳቦች፣ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በመጨረሻም የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ኢሳ ቦሩ ቦርዱ በሀገሪቱ የፋይናንስ እና የኢኮኖሚ ሥርዓት ጤናማነት ያለውን ከፍተኛ ሚና መረዳት ለሌሎች ተግባሮቻቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልፀው ለቦርዱ ዓላማ መሳካት እንቅፋት የሆኑ የህግ ክፍተቶችን ከተቀረው ቦርዱ ተጠሪ የሆነለት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ጋር በመሆን ለመፍታት የሚሰራ እና በሚመለከተው ሁሉ በቅርበት ለመደገፍ አቅም ያለው መሆኑን አብራርተዋል፡፡