የህጎች ማሻሻያ ዎርክሾፕ ተከናወነ

የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ በዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች ትግበራ አዋጅ 847/2006 እና የቦርዱን ተግባራት ለመወሰን በወጣው የሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁጥር 332/2007 ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ማዶ ሆቴል ታህሳስ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. የሙሉ ቀን የማሻሻያ ዎርክሾፕ አካሄደ፡፡

በዎርክሾፑ ላይ የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂዎች እና ኦዲት ሙያ ማኅበር፣ የኢትዮጵያ አካውንቲንግ ሶሳይቲ እና የውጪ ኦዲተሮች ማህበር የቦርድ አመራሮች እንዲሁም ከአማራ የተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂዎች እና ኦዲት ሙያ ማኅበር ተወካይ ተሳትፈዋል፡፡

በዕለቱም የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ እንደተናገሩት ህጎቹን ማሻሻል ያስፈለገው በተለይ የቦርዱ የባለፉት አምስት ዓመታት የስትራቴጂክ ዕቅድ አፈፃፀም የነበሩ ውሱንነቶችን በመቀነስ እንደ ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት መተግበር የሚገባቸው እና የሌሎችም ተቋማት የሚና መደበላለቅን በማስቀረት የአዋጁን ዋነኛ ዓላማ ለማሳካት የሚያስችል ሥራ ለመስራት እንዲያመች መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የህግ ማሻሻያ መርሃ-ግብሩን ያስተባባሩት የቦርዱ የህግ አገልግሎት እና ህግ ማስከበር ዳ/ት ዳይሬክተር አቶ ወርቁ አዲስ የህግ ማሻሻያ ስራው ረጅም ጊዜ የወሰደ ፣ ለቦርድ አመራር አባላትም ቀርቦ የነበረ እና የሙያ ማህበራቱም ቀድመው የተወያዩበት መሆኑን ጠቅሰው ከዎርክሾፑ በርካታ ግብዓቶች የተገኙበት እና ዓላማውን ያሳካ መድረክ ነው ብለዋል፡፡