የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም እና የቀጣይ 100 ቀናት ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ

የኢፌድሪ የገንዘብ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት  አፈፃፀም እና የቀጣይ 100 ቀናት ዕቅድ ግምገማ ሁሉም የሥራ ሓላፊዎች እና የቡድን መሪዎች በተሳተፉበት ህዳር 07 እና 08 ቀን 2014 ዓ.ም በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የስብሰባ አዳራሽ ውይይት አካሄዱ፡፡

በመድረኩም የቦርዱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር የቦርዱን የሩብ ዓመት አፈፃፀም እና የቀጣይ መቶ ቀናት እቅድ አቅርበዋል፡፡ በዚህም የፋይናንስ ሪፖርት ጥራትን በማስጠበቅ የህዝብን ጥቅም ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የፋይናንስ ሪፖርት እና የኦዲት ጥራት ግምገማ ለመጀመር የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውንና የማስፈፀሚያ መመሪያዎች ተግባራዊ መደረጋቸውን  አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም በቀጣይ 100 ቀናት ዕቅድ የውስጥ አቅም ግንባታ ተግባራት፣ ከተባባሪ አካላት ጋር የተጀመሩ ሥራዎችን በጊዜያቸው የማጠናቀቅ፣ ለኢንስቲትዩት ምስረታ የሚያስፈልጉ በሂደት ያሉ ተግባራትን እየተከታተሉ ማስፈፀም እና ሌሎችንም አቅርበው ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

በመጨረሻም የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ እንደተናገሩት ሀገራችን ያጋጠማት የሰላም መደፍረስ ባለበት የተመዘገቡ ዘርፈ-ብዙ ውጤቶች የተቀረፁ ሀገር-በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ለሌሎችም ፖሊሲዎቻችን ውጤታማነት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይም ለሰራተኞችም ሆነ ለተጠቃሚው የሚመጥን ምቹ የሥራ አካባቢ የመፍጠር ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸው፣ ሁሉም ተቋማት ዕቅዶቻቸውን በጥብቅ ዲሲፕሊን መምራት እና አቅምን አሟጠው መጠቀም እንዲሁም የተጓደሉትን በቀጣይ ሩብ ዓመት ማሳካት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይም ሁሉም ሠራተኛ ከበፊቱ በተሻለ መልኩ አንድነቱን በማጠናከር ሀገራችንን ከውስጥ እና ከውጪ ጫና ለማዳን በየተሰማራበት የሥራ ድርሻ ውጤታማነቱን ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡