የሰባት ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ ተካሄደ

የኢትየጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የ2013 በጀት ዓመት የሰባት ወራት የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ ከሁሉም ሰራተኞች ጋር ከየካቲት 19 እስከ 21 ቀን 2013ዓ.ም በአዳማ ከተማ አከናወነ፡፡

የዉይይት መድረኩን የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር አማካሪ አቶ ወርቁ ዓለሙ የከፈቱት ሲሆን የ2013 በጀት ዓመት እቅድ የቀድሞዉ አምስት ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድ እና ፍኖተ ካርታ ተጠናቆ የቀጣይ አምስት ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድ ዝግጅት ላይ ባለበት ሆኖ በ2013 በጀት ዓመት ለቦርዱ የዝግጅት ወቅት መሆኑን በማዉሳት አፈፃፀሙም በዚሁ አንፃር የሚገመገም መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የአፈፃፀም ሪፖርቱ በቦርዱ የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት በኩል የቀረበ ሲሆን ሪፖርቱ የዉጤት ተኮር አፈፃፀም ምዘና ስርዓት ተከትሎ የተከናወኑና ያልተከናወኑ ተግባራት ፣ያጋጠሙ ችግሮች ፣የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች እና ቀጣይ አቅጣጫ ያካተተ ነዉ፡፡

በቀረበዉ የአፈፃፀም ሪፖርትም ከሰራተኞች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበዉ ዉይይት የተካሄደባቸዉ ሲሆን የታዩ ጠንካራ ጎኖች ተጠናክረዉ የሚቀጥሉበት፣ ደካማ ጎኖችን በማስወገድ እና መሻሻል ያለባቸው አሰራሮች ተሸሽለው መፍትሔ በሚሹ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት እንደሚገባ ተስተዉሏል፡፡

በተለይ የሰራተኛ መጠነ-መልቀቅ ምክንያቶችን በተገቢዉ መለየት እና መፍትሄ ስለማበጀት እንዲሁም ቦርዱ የተቋቋመበትን ዋና ዓላማ ከማሳካት አንፃር የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ የመዋቅር ማሻሻያ እየተሠራ መሆኑ፣ ከሌሎች ተባባሪ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰሩ ያሉ የቀጣይ አምስት ዓመታት ስትራቴጂያዊ እቅድ ዝግጅት፣ ከACCA ኢትዮጵያ ጋር እየተሰሩ ያሉ በርካታ የአቅም ግንባታ እና የማማከር ስራዎች ተስፋ ሰጪ ተግባራት መሆናቸዉን የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ አስረድተዋል፡፡

በግምገማ ቆይታዎቹም ስለ ቡድን (team)፣ የቡድን አወቃቀር እና የቡድን ስራ ምንነት ላይ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን  የቦርዱ አገልግሎት አሰጣጥ ለዉጥ ፍኖተ ካርታ ማስፈጸሚያ ስልት ቀርቦ ሰፋ ያሉ ዉይይቶች ተካሂደዋል ፡፡

የበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራትንም አመራሩና ሰራተኛዉ በመናበብ እና እጅ ለእጅ በመያያዝ ቢያንስ ከ75% እስከ 80% ግቦቹን ለማሳካት ቁርጠኝነት የታየበት መድረክ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል፡፡