ማንኛውም የሂሣብ ሙያ አገልግሎት ወይም የኦዲት አገልግሎት ድርጅት ለምዝገባ ማመልከት እንዳለበት የቦርዱ ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 332/2007 አንቀጽ 20 ይደነግጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማንኛውም ፐብሊክ ኦዲተር በራሱም ሆነ ከሌላ ሰው ጋር በሽርክና ቦርዱ ስሙን ባላፀደቀው የኦዲት ድርጅት ስም እንደ ኦዲተር ሆኖ መሥራት እንደማይችል አዋጅ ቁጥር 847/2006 አንቀጽ 21 ይደነግጋል፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ሂሣብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የአዋጁና ደንቡ ማስፈፀሚያ መመሪያ እስከሚወጣ ድረስ ቀደም ሲል የሙያ ፈቃድ ያወጡ የኦዲት ድርጅቶች ይገለገሉበት የነበረውን የንግድ ስም ስያሜ በመመዝገብ በድህረ ገፁ በማውጣት በጊዜያዊነት ሲያስተዋውቅ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

ነገር ግን ቦርዱ የደንብ ቁጥር 332/2007 እና አዋጅ ቁጥር 847/2006 ማስፈፀሚያ መመሪያ እስከሚወጣ ድረስ ኦዲተሮችን በጊዜያዊነት ያስተዋውቅበት የነበረውን የንግድ ስም ስያሜ ከንግድ ህጉና የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 ጋር በተጣጣመ መልኩ ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ስለዚህ ከስማችሁ በተጨማሪ በሸርክና ማኀበር (General Partnership, Limited Partnership) እና ጓዶቹ (& Co/ Company/ Associate) ሆነ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር (PLC) በሚል የተመዘገባችሁ የሂሣብ ሙያ አገልግሎት ወይም የኦዲት አገልግሎት ድርጅቶች ይህ ማስታወቂያ በቦርዱ ድረ-ገጽ ከወጣበት ቀን አንስቶ የተመዘገበና የፀደቀ የመመስረቻና መተዳደሪያ ፅሑፍ ይዛችሁ በመቅረብ የንግድ ስም ስያሜ ምዝገባ እንድታደርጉ እያሣሰበ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ማሥረጃዎቹን ይዘው ያልቀረቡ በንግድ ስም ስያሜ የሚንቀሣቀሱ የሙያ ድርጅቶች የንግድ ስም ከቦርዱ የሙያ ፈቃድ አውጥተው የንግድ ምዝገባ ያላቸውን ባለሙያዎች ስም ብቻ በመጥቀስ የሚስተካከል መሆኑን እናሣውቃለን፡፡

የኢትዮጵያ ሂሣብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ