የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከአዲስ አበበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት አባለት/ሪፖርት አቅራቢ አካላት/ ጋር የምክክር መድረክ ተካሄደ

የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር ከምክር ቤቱ አባለት/ሪፖርት አቅራቢ አካላት/ ከሆኑ የንግዱ ማህበረስብ አካላት ጋር ታህሳስ 20/2015 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ፋይናንስ ሪፖርት ትግበራ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ በዲኦሎፖል ሆቴል የግማሽ ቀን የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡

ከ150 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት የተካሄደው የውይይት መድረክ የመሩት አቶ ፍቃዱ አጎናፍር የቦርዱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንደተናገሩት ዓለማቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ትግበራ ወጥነት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት ለማዘጋጀትና ድርጅቶችን ከውድቀት ለመታደግ እንደሚያግዝ እና በግልና በመንግስት ዘርፍ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በቦርዱ በተዘጋጀው መስፈርት መሰረት በተለይ የህዝብ ጥቅም ያለባቸው እና ሌሎች መስፈርቱ የሚመለከታቸው በርካታ ድርጅቶች ወደ ትግበራ መግባታቸውን የገለጹ ሲሆን በተለያዩ ምክንያት የተራዘመው የትግበራ ጊዜ በዚሁ አመት የሚጠናቀቅ በመሆኑ ድርጅቶቹ ያሉበትን ደረጃ ለማወቅና በወቅቱ ለማጠናቀቅ ይቻል ዘንድ የምክክር መድረኩ መዘጋጀቱ አብራርተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት የትግበራ አፈጻጸም ላይ የምክክር መድረክ የተገኙት የአዲስ አበባ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ዋና ፀሐፊ የሆኑት አቶ ሺበሺ ቤተማርያም ስለንግድ ምክርቤቱ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ትግበራ ኩባንያዎች ከሌሎች ዓለም አቀፍ አቻ ኩባንያዎች ጋር አብሮ ለመስራት የሚያችልና ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸው ኩባንያዎች ሲያሸንፉ ሀገራችን እንደምታሸንፍ አክለው አስረድተዋል፡፡

በዕለቱ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ሕጎች ላይ ሰፊ ግንዛቤ የተፈጠረ ሲሆን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ትግበራ የተሟላ፣ ግልጽና ወጥነት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ሥርዓት የሚያደርግ በመሆኑ ግልጽነትና ተጠያቂነትን እንደሚያጎለብት ተብራርቷል፡፡ እንዲሁም የሪፖርት አቅራቢዎች የሪፖርት ማቅረቢያ ጊዜዉን እና የመለያ መስፈርቶቹን በዝርዝር ቀርቧል፡፡

በመጨረሻም ቦርዱ ባወጣው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ትግበራ ፍኖተ-ካርታ መሰረት የህዝብ ጥቅም ላለባቸው እስከ 2015 በIFRS እና አነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች እስከ 2016 ዓ.ም. በIFRS for SMEs መሆኑን አውቀው ወደ ትግበራ ያልገቡ ሪፖርት አቅራቢ አካላት በዚሁ መሰረት እንዲያቀርቡ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡