የክልል የመንግስት የልማት ድርጅቶች IFRS ስልጠና ተጀመረ፡፡

***********************************************************

የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ከመጋቢት 6-8/2015 ዓ.ም. የሚቆይ የIFRS ትግበራ የግንዛቤ ማስጨበጫ በዲ-ሌኦፖል ሆቴል ለክልል መንግስታት የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

የግንዛቤ ማስጨበጫው ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች ትግበራን አስመልክቶ ሪፖርት አቅራቢ አካላት ዓመታዊ የሂሳብ መግለጫቸውን በ’IFRS’_ መሠረት እንዲዘጋጁ እና በወቅቱ ለቦርዱ እንዲያቀርቡ ለማስቻል ሲሆን በሥልጠናው ከአፋር፣ ከሲዳማ፣ ከደቡብ ምዕራብ እና ከትግራይ ክልል የመንግስት የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች  ውጭ የሁሉም ክልል የመንግስት የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው፡፡

በዕለቱ የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ በመክፈቻ ንግግራቸው በኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ የ”IFRS” ትግበራ  በመንግስት የልማት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ መተግበር ያለበት መሆኑን ጠቅሰው ለክልል የመንግስት የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ ኃላፊዎች እና  ባለሙያዎች በዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ደረጃዎቹ ላይ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የአቅም ግንባታ ስራ መስራት ማስፈለጉን ገልጸው  የግንዛቤ ማስጨበጫውም ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በዘርፉ ልምድ  ባላቸው ባለሙያዎች የሚሰጥ በመሆኑ ተሳታፊዎች ለትግበራው ውጤታማነት የተሻለ ግንዛቤ እንደሚጨብጡም ተናግረዋል፡፡

በመድረኩም 150 የክልል የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን የIFRS ፅንሰ-ሃሳብን እና አተገባበሩን በምሳሌዎች በማስደገፍ በተሳታፊዎች የቡድን ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

ስልጠናው ከየካቲት 28/2015ዓ.ም ጀምሮ ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታ እና አስተዳደር፣ ለኢንስትመንት ሆልዲንግስ፣ ለአዲስ አበባ ተጠሪ የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እንዲሁም ለኢንሹራንስ ኦዲተሮች በተመሳሳይ የተሰጠ መሆኑ ይታወሳል፡፡