የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ክንውን እና የ2015 ዕቅድ ግምገማ ተከናወነ፡፡                                         

የገንዘብ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ሐምሌ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ የግማሽ ቀን ውይይት አደረጉ፡፡

ውይይቱን የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የመሩት ሲሆን የግምገማው ዓላማ ሀገራችን ከተጋረጡባት ጫናዎች አንፃር በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማት የተከናወኑት ተግባር ለቀጣዩ ዕቅድ ግብዓት እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡

በዕለቱም የቦርዱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር የቦርዱን የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2015ን ዕቅድ ያቀረቡ ሲሆን በተለይ የፋይናንስ ሪፖርት እና የኦዲት ጥራት ማረጋገጥ ምርመራዎች መጀመራቸው፣ የውስጥ እና የውጭ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስራዎች፣የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ምስረታ ጅማሮ፣ የስትራቴጂያዊ አጋርነት አመራር ተግባራት እና ሌሎችም የቦርዱ ዋነኛ አፈፃፀሞች መሆኑን ያቀረቡ ሲሆን ያልተከናወኑ እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንም በስፋት አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይም የቀጣይ 2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት በተለይ ከተጀመሩት የፋይናንስ ሪፖርት እና የኦዲት ጥራት ማረጋገጥ ምርመራዎችን ተከትሎ የሚከሰቱ የህግ ጥሰቶችን ለመከላከል እና ህጉን ተላልፈው በሚገኙት ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ክቡር ሚኒስትሩ የተቋማቱ የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀም ውጤታማ እና አበረታች መሆኑን እንዲሁም የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ሀገራዊ ራዕዩን ለማሳካት ከፍተኛ ትርጉም እንደሚኖረው እና ዕቅዱ በጥብቅ ዲሲፕሊን መመራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡