ለመንግስት የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች የIFRS ሥልጠና መስጠት ተጀመረ

የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ለተውጣጡ 59 የፋይናንስ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ከመጋቢት 12-16/2014 ዓ.ም ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የIFRS ስልጠና በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መስጠት ጀመረ፡፡

በዕለቱም የቦርዱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር እንደተናገሩት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉልህ የህዝብ ጥቅም ያለባቸው ሪፖርት አቅራቢ አካላት ሆነው በፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች መሠረት የሂሳብ መግለጫቸውን አዘጋጅተው ወደ ቦርዱ እንዲያቀርቡ በመጀመሪያው ፍኖተ ካርታ የተለዩ ቢሆንም አብዛኞቹ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተገበሩ እና በትግበራ ሂደት ያሉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሆኖም በተሻሻለው ፍኖተ ካርታ መሠረት ወደ ትግበራ ያልገቡ እነኚህ አካላት የ2015ዓ.ም የሂሳብ መግለጫቸውን በፋይናንስ ደረጃዎች (Full IFRS) መሠረት አዘጋጅተው ወደ ቦርዱ ማቅረብ እንዳለባቸው እና ለዚህም የውስጥ አቅም ግንባታው አስፈላጊ በመሆኑ ስልጠናው ከዓለም ባንክ ግሩፕ ጋር በመተባበር ተዘጋጅቶ የሚሰጥ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

ስልጠናው በቨርቹዋል (Virtual meeting) ሁለት ባለሙያዎች ከለንደን በቀጥታ እና በቦርዱ የሙያ አማካሪ አቶ አሸናፊ ጌታቸው በአካል የሚሰጥ ይሆናል፡፡

ሥልጠናው በቀጣይም ከመጋቢት 18-22/2014 ዓ.ም ለአምስት ተከታታይ ቀናት ለቀሩት የመንግስት የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በተመሳሳይ ሁኔታ የሚሰጥ ይሆናል፡፡