2014 በጀት ዓመት ክንውን2015 ዕቅድ እና መዋቅራዊ አደረጃጀት ላይ ውይይት ተካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ሠራተኞች በ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ክንውን፣ በ2015 ዕቅድ እና መዋቅራዊ አደረጃጀት ላይ ሐምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም በቦርዱ የስብሰባ አዳራሽ የግማሽ ቀን ውይይት አካሄዱ፡፡

በውይይቱም የቦርዱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር እንደተናገሩት የ2014 በጀት ዓመት ከአስር ዓመቱ ስትራቴጂያዊ እቅድ አንፃር መሰረታዊ የሚባሉ ቦርዱ ለማሳካት የተቋቋመባቸው ተግባራት የተጀመሩበት መሆኑን ጠቅሰው አፈፃፀሙን መገምገም የ2015 ዕቅዳችንን ለማሳካት ከፍተኛ ትርጉም ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በዚሁም መሰረት የቦርዱ የስትራቴጂክ እቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳ/ት ዳ/ር አቶ አልታሰብ አየሁ የ2014 በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራት፣ ያልተከናወኑ፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፣ የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎችንና የወደፊት አቅጣጫዎችን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን የ2015 ዕቅድም ቀርቦ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በእቅዱም የሂሳብና ኦዲት ሪፖርት ጥራት ምርመራ፣ የሪፖርት አቅራቢ አካት ምዝገባና የሙያ ፍቃድ አሰጣጥን ማሻሻል፣ የህግ አፈጻጸምን ማሳደግ፣ የሂሳብና ኦዲት ደረጃዎችን ማሳደግ እንዲሁም ስትራተጂካዊ አመራርና አጋርነትን ማጠናከር ዋና ዋና የትኩረት መስኮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በውይይቱም የፋይናንሻል ሪፖርት እና ኦዲት ጥራት ማረጋገጥ ምርመራ፣ ህግን ባላከበሩ ባለሙያዎች እና ግለሰቦች ላይ የተወሰዱ አስተማሪ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተተገበሩ የቅንጅት ስራዎች እና የአቅም ግንባታ ስራዎች በዋነኝነት የሚጠቀሱ ውጤታማ ተግባራት መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን ቦርዱ የተቋቋመበትን ዋና ዓለማ በማሳካት ደረጃ እያመጣ ያለው ውጤት አበረታች በመሆኑ አጠናክረን መቀጠል ይገባናል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የሙያ ፍቃድ አሰጣጥ እና እድሳት አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥነት እንዲኖረውና ከክልሎች ጋር እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ የሠራተኛ ማበረታቻ ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ተጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል ቦርዱ ባዘጋጀው መዋቅር መሰረት የሠራተኞች ድልድል ጋር በተያያዘ የቦርዱ የሰው ሀብት ልማትና አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረሰ መለሰ የፌዴራል መንግስት መሥሪያ ቤቶች መዋቅራዊ አደረጃጀት መመሪያ ቁጥር 859/2014 ላይ ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል፡፡ በመመሪያው አተገባበር ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት ተከሂዶ ስድስት አባላት ያሉት የድልድል ኮሚቴ እና አራት አባላት ያሉት የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በማቋቋም የድልድል ሥራው በአጠረ ጊዜ ውስጥ በማከናወን ወደ ተግባር መገባት አለበትም ተብሏል፡፡

በመጨረሻም የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂከመት አብደላ በ2014 የታዩ ጠንካራ ጎኖችን፣ የተጀማመሩ አበረታች ተግባራትን በማጠናከር እና ክፍተቶችን በማረም የ2015 ዕቅድን በውጤታማነት ለመተግበር በሙሉ ተነሳሽነት እና በባለቤትነት መንፈስ መነሳት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡