ለሴት የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች የሕይዎት ክህሎት ማነቃቂያ ስልጠና ተሰጠ፡፡
************************************************************************
መጋቢት 10/ 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የሴቶችን የስራ እና የግል ህይወት ሚዛናዊነት ማስጠበቅ; በሚል መሪ ሀሳብ መጋቢት 9እና 10 ቀን 2015 ዓ.ም በደብረ-ዘይት ከተማ ለቦርዱ ሴት የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች የሕይወት ክህሎት ማነቃቂያ ስልጠና ሰጠ፡፡
የስልጠናው ዓላማ ሴቶች በቤተሰብ አስተዳደር ሚናቸው በተጨማሪ ከቤት ውጪ ባላቸው የህዝብ አገልጋይነት እና የግል ህይወታቸውን ሚዛናዊነት በመጠበቅ በተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ውጤታማ እንዲሆኑ ማብቃት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
በዕለቱ የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደተናገሩት በቦርዱ የሴቶች የመሪነት ስብጥር አነስተኛ መሆኑን ገልጸው በተለይ በርካታ የሥራው ዓለም ተግዳሮቶች እና የቤተሰብ አመራር ተደራራቢ ኃላፊነት ያሉባቸው ሴቶች በተሰማሩበት የስራ መስክ ጤናማ የመሪነት ሚናቸውን በብቃት መወጣት እንዲችሉ ማበረታታት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ስልጠናውን የሰጡት በመስኩ አስልጣኝ የሆኑት ወ/ሮ ፍጹም ኪዳነማሪያም ሴቶችን ማብቃት ቤተሰብ ላይ መስራት መሆኑን ገልጸው የስራ እና የግል ህይወት ሚዛናዊነትን ማስጠበቅ በእቅድ እንድንመራ እና የምንሰራውን ስራ በመውደድ ውጤታማ እንድንሆን ያስችለናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በስልጠናው ወ/ሮ ፍጹም እና ሌሎችም የህይወት ተሞክሯቸውን ያካፈሉ ሲሆን በስልጠናው የተሳተፉ ሴት ሰራተኞቹም የስራ እና የግል ህይወት ሚዛናዊነትን በማስጠበቅ ውጤታማ እና ጤናማ ህይወት ለመኖር የሚያስችል ግንዛቤ እንዳገኙ እና መነቃቃት እንደፈጠረላቸው አውስተው መሰል ማነቃቂያዎች ተጠናክረው መቀጠል ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
በመጨረሻም ዋና ዳይሬክተሯ ሴቶች በሁለንተናዊ የሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ተሳትፎአቸውን በማሳደግ ለውጤት ማብቃት የሚቻለው አስፈላጊ ድጋፎች እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በየወቅቱ ለመተግበር ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይ ክፍተትን መሰረት ያደረጉ ተመሳሳይ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ዕቅድ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡

Exif_JPEG_420
Leave A Comment
You must be logged in to post a comment.