ለፋይናንስ ተቋማት የሚቀርቡ የኦዲት ሪፖርቶችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ እንደሚስፈልግ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ለፋይናንስ ተቋማት በሚቀርቡ የኦዲት ሪፖርቶች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ከግል ባንኮች እና ከኦዲት ድርጅቶች ማህበራት ከተወከሉ አመራሮች ጋር ህዳር 02 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በዲኦሎፖል ሆቴል የግማሽ ቀን የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡

የቦርዱ ምክትል ዋና ዳይሬከተር አቶ ፍቃዱ አጎናፍር በመክፈቻ ንግግራቸው እንደጠቀሱት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ቦርዱ የሚቀርቡ የሂሳብ መግለጫዎች አጠራጣሪነት እና እነዚህ ሪፖርቶች ወደ ባንኮችም በተለያየ መልኩ እየመጡ መሆን በቀጣይ እነኚህ ሀሰተኛ የኦዲት ሪፖርቶችን በጋራ መከላከል የሚቻልበት ጉዳይ ላይ በጋር መወያየት አስገዳጅ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በዕለቱም የቦርዱ የህግ ማስከበር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወርቁ አዲስ በፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ህጎች ላይ እና ከኦዲት ሪፖርት ዝግጅት ጋር እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች ላይ የመነሻ ፅሁፍ አቅርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወክለው ተገኙት የባንኩ principal Bank Exminer  አቶ በለተ ፎላ በበኩላቸው ህገወጥ አካሄዶችን ከመከላከል አንፃር አንድ ድርጅት የሚያቀርበው የፋይናንስ ሪፖርት የድርጅቱን ህልውና የሚያሳይ በመሆኑ ማንኛውም ባንክ ብድር ከመስጠቱ በፊት የፋይናንስ ሪፖርቱን በመገምገም የድርጅቱን ጤናማነት ማረጋገጥ ይገባዋል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ የሒሳብ አያያዝ ሙያ (Accountancy Profession) ከተጠናከረ ለሀገር የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ ቦርዱ ከብሔራዊ ባንክ እና ከኦዲት ድርጅቶች ማህበራት ጋርም በጋራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡