የተከበሩ ወ/ሮ ለምለም ሐድጎ፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣
የተከበራችሁ የሀገራችን የሚዲያ አካላት ተወካዮችና የዚህ መድረክ ተሳታፊዎች፣
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት የስራ ሃላፊዎችና የዚህ መድረክ አዘጋጆች፣
የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የሥራ ሓላፊዎች፣
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች፣
ክቡራትና ክቡራን፤
ከሁሉ በፊት በዛሬው ዕለት ጥሪያችንን አክብራችሁ ስለመጣችሁ የተሰማኝን ታላቅ ክብርና ደስታ በመግለጽ እንኳን በሰላም መጣችሁ እያልኩ በዚሁ አጋጣሚ ለሁሉም የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለገና በዓል በሰላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡
ከፍተኛ ጥራት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎችን ከመተግበር አንጻር የቀድሞውን አሰራር በተለይ ከወጥነትና በዓለማቀፍ የአቀራረብ ይዘቱ ከሀገር ሀገር ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ከ160 በላይ የዓለም ሀገራትና ተቋማት ወደ ትግበራ ከገቡ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ትክክለኛ የፋይናንስ መረጃ አቅርቦት ለሀገር ኢኰኖሚ ዕድገት፣ ለግልጽነትና ተጠያቂነት፣ ለሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ለህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትና ለፍትሐዊነት የሚያበረክተው ፋይዳ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ እንደሀገራችን ገና በዕድገት ላይ ላሉት ደግሞ ያላቸውን ውሱን ሀብት ተገቢው ዓላማ ላይ በማዋልና ውጤቱንም ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን በጠበቀ፣ ከፍተኛ ጥራት ባለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች በመታገዝ መጠየቅ ለሚችለው ብቻ ሳይሆን መጠየቅ ለማይችለው ግን ደግሞ መረጃውን የማግኘት መብትም ፍላጎትም ላለው ሰፊው ሕብረተሰብ ለማድረስ ስርዓቱን መተግበር ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡
ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን በሀገር እና ወገን ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን ላለፉት 10ት አመታት ዓለምን ያጋጠመው የፋይናንስ ቀውስ የዚሁ መገለጫ መሆኑንና በሀገራችንም የፋይናንስ ስርዓት ጤናማነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥራት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎችን መተግበር ጊዜ የማይሰጠው መሆኑን ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡
ክቡራን የመድረኩ ተሳታፊዎች
የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ሥርዓት የተመቸ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ በመፍጠርና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት የሚኖረውን ከፍተኛ ጠቀሜታ፣ እንዲሁም የተጠናከረ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ሙያ የኢኮኖሚ ዕድገቱን በመደገፍ፣ በማበረታታት እና በማረጋጋት የሚጫወተውን ቁልፍ ሚና በመገንዘብ በሀገር ውስጥ በሚገኙ በግል፣ በመንግስት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ ተፈፃሚ የሚሆን “የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ” አዋጅን በ2006ዓ.ም አውጥቷል፡፡
አዋጁንም የሚያስፈፅም “የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ” በሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ የተቋቋመ ሲሆን አዋጁ በተለያዩ የሪፖርት አቅራቢ አካላት ላይ ተፈፃሚ የሚሆኑ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ማዕቀፎችን በማስቀመጥ ሙያውን በበላይነት የመምራት፣ የመቆጣጠርና የማሳደግ ኃላፊነት ለቦርዱ ሰጥቷል፡፡
ቦርዱም ተቆጣጣሪ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሆኖ በህግ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለተልዕኮዎቹ ማስፈፀሚያ ያስቀመጣቸውን አምስት ዋና ዋና የትኩረት መስኮች መሠረት በማድረግ የውስጥ አቅሙን በሂደት በማጠናከር እና በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ላለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፤በማከናወንም ይገኛል፡፡
የተከበራችሁ ተሳታፊዎች
ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ሥርዓት ትግበራ ለሀገራችን አዲስ ፍልስፍና እንደመሆኑ መጠን ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ተግዳሮቶቹ ብዙ ናቸው፡፡ በብዛትም ሆነ በጥራት የተሟላ የሰው ሃይል እጥረት፣ የሁኔታዎች አለመመቻቸትና ሌሎች ውስጣዊ ተግዳሮቶችን ያለውን አቅም ሁሉ አሟጦ በመጠቀም ማካካስ ቢቻልም አብዛኞቹ ውጫዊ ተግዳሮቶቹ ግን በቀላሉ ሊታለፉ የሚችሉ አልነበሩም፡፡ ለምሳሌ ያክል
- አሁን ያለንበት የሀገራችንን የኢኮኖሚ ዕድገትን መሸከምና ማስተናገድ የሚችል ባለሙያ ገበያ ላይ አለመኖር፣
- በትምህርት ተቋማት ደረጃ የሚሰጠውና ወደ ተግባር ሲገባ ያለው እውነታ አለመገናኘት፣
- ሪፖርት አቅራቢ አካላትና የድርጅቶች አመራሮች ሀሳቡን በተገቢው ተረድተው ወደ ተግባር አለመግባት ዳተኝነት፣
- ከሚፈልገው ሥነ-ምግባር ውጪ የሚንቀሳቀሱ አካላት መኖርና በውጤቱም የህዝብን ጥቅም የሚጎዱ ግለሰቦች/ድርጅቶች መኖር፣ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች ቢሆኑም
- የሚዲያውን ተገቢ የሆነ ሙያዊ እገዛ ማጣት ደግሞ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል፡፡
ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ለመቅረፍ በእናንተ የትክክለኛ የመረጃ ምንጭነት፣የማስተማርና የማሳወቅ ተግባራት እና ከቦርዱ ጋር በምትፈጥሩት ቅንጅታዊ አሰራር ጥራት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ እውን እንዲሆን የፋይናንስ ትክክለኛ መረጃን ለሁሉም አካለት ተደራሽ ማድረግ ወሳኝ በመሆኑና በዛሬው እለትም ለአተገባበሩ ከመግባባት እንደምንደርስ ሙሉ እምነቴ መሆኑን እየገለጽኩ ለምትፈልጉት መረጃም ሁሉም የሥራ ክፍሎቻችን የእናንተን መምጣት ክፍት ሆነው ይጠባበቃሉ።
ክቡራንና ክቡራት
የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከላይ በጠቃቀስናቸውና ሌሎችም ተግዳሮቶች ታጅቦ ያለ ቢሆንም ተግዳሮቶችን እንደ እንቅፋት ሳይሆን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል፤ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ለአብነትም
- ለዩኒቨርስቲ የዘርፉ ምሁራን የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የአሰልጣኞች ስልጠና ስራ፣ እንዲሁም ለምረቃ የደረሱ ተማሪዎቻቸው የ2 እና 3 ወራት ሥልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ስራው ዓለም ሲገቡ በቀላሉ መላመድ የሚያስችላቸው ስራ የመሥራት፣
- የትምህርት ሥርዓቱ አካል እንዲሆን ከሚመለከታችው አካላት ጋር የመስራት፣
- ከ2 ወር እስከ 40ዎቹ ዓመታት ዕድሜ እና በጣት ከሚቆጠሩ እስከ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ አባለት ያሏቸው በልምድ የሚንቀሳቀሱ የሙያ ማህበራት የደረጃዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው፣ ተጠናክረው የአባሎቻቸውን መብት እና የሙያውን ነፃነት እንዲያስከብሩ፣ የህዝብን ጥቅም እንዲያስጠብቁና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገትም የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ የማስገንዘብ ሥራዎች ፣
- አሰራሩ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን የማድረግና የተሻለ ልምድ ካላቸው መሰል ሀገራት ተሞክሮዎችን በመውሰድ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ማጠናከርና ተግባር ላይ የማዋል ስራዎች፣
- ቦርዱ ህጋዊነትን ለማበረታት በሚጥረው ልክ ህገወጥነትን በሚከተሉ አካላት ላይ አስተማሪ የሆነ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምቶች የመውሰድ ሥራዎች፣
- ከባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ የግንኙነት ሥርዓት መዘርጋት የተቻለ ሲሆን ለትግበራውም ምቹ ሁኔታ የመፍጠርና ወደ ተግባር የማስገባት ስራዎች፣
- የዘርፉ ባለሙያዎችና አገልግሎቱን የሚሰጡ ድርጅቶች ቁጥር በጥራትም በብዛትም ከቀን ቀን እንዲጨምር በተሰራው ስራ አበረታች ውጤቶች መታየት መጀመር፣
- ወደ ተግባር የገቡ ከፍተኛ የህዝብ ጥቅም ያለባቸው ተቋማት ተከታታይነት ያለው የድጋፍና የክትትል ሥራዎች መሰረት ውጤቱንም ማየት የተጀመረ መሆኑ በጥቂቱ የሚጠቀሱ የቦርዱ ስኬቶች ናቸው፡፡
ለዚህም ቦርዱ ከምስረታው ጀምሮ ተልዕኮውን ለማሳካት መረጃን ተደራሽ ለማድረግ በጠየቅናችሁ ጊዜያት ቀና ምላሽ ለሰጣችሁን ኩራትና ክብር እየተሰማኝ ለስርዓቱ ሙሉ በሙሉ ትግበራ መሰረታዊ እና እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ህዝብን የማሳወቅ ስራችሁን ለመከወን እዚህ በመገኘታችሁ በድጋሚ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።
ክቡራትና ክቡራን
የሀገራችን የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ሥርዓት ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተዘጋጅቶ በመረጃው ተጠቃሚ አካላት ዘንድ አመኔታ የሚጣልበት፣ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማሳደግ ድህነትን ለመዋጋትና ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ እናንተም ሙያዊና ሀገራዊ ሐላፊነት አለባችሁ ብዬ አምናለሁ፡፡
ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ሙያችሁና የተቋማችሁ ተልእኮ በዋነኝነት ህግና ስርአት ተከብሮ የህዝብ ጥቅም ከዘርፉ እንዲረጋገጥ ማድረግ ከቦርዱ ጋር የምትጋሩት መሆኑን በመረዳት በዛሬው ውይይታችን ንቁ ተሳትፎ እንድታደርጉና ለቀጣይ ተግባርም የተሸለ ስንቅ የምትሰንቁበት መድረክ እንደሚሆን እየተማመንኩ መልካም የውይይት ጊዜ እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡
አመሰግናለሁ!!
Leave A Comment
You must be logged in to post a comment.