boardየኢትየጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጋር በመተባበር “አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብን ለማስተዋወቅ የመገናኛ ብዙሀን የማይተካ ሚና አላቸው” በሚል መሪ ቃል የሁሉም የሀገር ውስጥ የመንግስትና የግል የሚዲያ ተቋማት በማሳተፍ በአዲሶቹ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች አተገባበር ላይ ግንዛቤን የሚፈጥር የሚዲያ ፎረም ጥር 2 እና 3 ቀን 2012ዓ.ም በአዳማ ከተማ  ድሬ ኢንተርናሽናል ሆቴል አካሄደ።

የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸውን ካቀረቡ በኋላ ጥራት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ በሀገራችን በሁሉም የግል፣ የመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ተግባራዊ እንዲሆን ቦርዱ እየሰራ እንደሚገኝና የመገናኛ ብዙሀኑ ለህዝብ ለማስተዋወቅና ግንዛቤ ለመፍጠር የማይተካ ሚናቸውን እንዲወጡ ፎረሙ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

በመቀጠልም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ  ክብርት ወ/ሮ ለምለም ሓድጎ የኢፌዲሪ መንግስት አለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎችን መተግበር ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት ያለውን ፋይዳ በመረዳት በአዋጅ ቁጥር 847/2006 መደንገጉን አስታውሰው ከቦርዱ በተጨማሪ የሚዲያ አካላትም በደረጃዎቹ አተገባበር ዙርያ በእውቀት ላይ የተመሰረ መረጃን ተደራሽ በማድረግና በህዝብ ዘንድ ግንዛቤን ለመፍጠር መድረኩ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዕለቱም አቶ ልኡል ዘውዴ(FCCA) እና አቶ ጌቱ ጀማነህ(FCCA) ከቦርዱ መቋቋም በፊት በሀገራችንና በአለም አቀፍ ደረጃ የነበረ የፋይናንስ ሪፖርት አያያዝ ስርአት ታሪካዊ ዳራ እንዲሁም አዋጁ እንዲወጣና ቦርዱ እንዲቋቋም አስገዳጅ የሆኑ ሁኔታዎችን፣አቶ ደመላሽ ደበሌ ቦርዱ ከተቋቋመ በኋላ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ አቶ ወርቁ አዲስ፣አቶ ቶማስ ሙሉጌታ(FCCA) እና አቶ ታዬ ፈቃዱ (ACCA) በደረጃዎች ትግበራ ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫን የተመለከቱ የመወያያ ጽሁፎች ያቀረቡ ሲሆን በሁለተኛው ቀን በአፈጻጸሙ ወቅት የሚዲያው ሚናን የተመለከተ የመነሻ ጽሁፍ በአቶ ታምራት ወ/ጊዮርጊስ የፎርቹን ጋዜጣ ዋና አርታኢ ቀርቦ በሁሉም ሰፋ ያለ ውይይት  ተካሂዶበታል።

በውይይቱ ማጠቃለያም በቅንጅት በመስራት የህዝብ ጥቅም እንዲረጋገጥና ተቋማት ከውድቀትና ከኪሳራ ስጋት መዳን እንዲችሉ የሚዲያ ፎረም ሙያዊ ሓላፊነታቸውን መወጣት እንዲችሉ ሁሉም ተሳታፊ አካላት ከመግባባት ላይ ደርሰው ከቦርዱ፣ከኢዜአና ከሚዲያ አካላቱ የተውጣጣ ፎረም ተቋቁሞ ወደስራ መግባት እንደሚገባ መስማማት ተችሏል።