የሪፖርት አቅራቢዎች መለያ መስፈርት እና የሪፖርት ማቅረቢያ ጊዜ ማሻሻያ ይፋ ሆነ

የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ጉልህ የህዝብ ጥቅም ያለባቸው፣ ሌሎች የህዝብ ጥቅም ያለባቸው፣ አነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች መሠረት የፋይናንስ ሪፖርታቸውን የሚያቀርቡበትን ጊዜእና የመለያ መስፈርቶችን ማሻሻሉን ነሐሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ገንዘብ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አደረገ፡፡

ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ እንደተናገሩት የሀገሪቱን የፋይናንስ ሥርዓት ጤናማነት ለማረጋገጥ መንግሥት እየወሳደቸው ካሉ ሪፎርሞች አንዱ የሆነው በግል፣ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በመንግስት ሥር በሆኑ የልማት ድርጅቶች እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ ተፈፃሚ እየተደረገ ያለው ዓለም-ዓቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

መንግሥት ደረጃዎቹን በማስተግበር ድርጅቶች በዓለም ዓቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እና ኢንቨስትመንትን በመሳብ ድህነትን ለመቅረፍ በሚደረገው ትግል የድርሻቸውን እንዲወጡ ህግ ያወጣ ሲሆን ይህንንም በሚመራ ቦርድ ላለፉት አራት ዓመታት ጠንካራ ሥራዎች የተሰሩ ቢሆንም በተለያዩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች የተጠበቀውን ያክል ባለመሆኑ የሪፖርት አቅራቢ አካላት የመለያ መስፈርት እና የማቅረቢያ ጊዜ ማሻሻል ማስፈለጉን አውስተዋል፡፡

በመጨረሻም ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂክመት አብደላ እንደተናገሩት ቦርዱ በቀጣይ ተልዕኮውን ለማሳካት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በርካታ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለመሥራት በዝግጅት  ላይ መሆኑን ገልፀው የጊዜ ማሻሻያው የህዝብ ጥቅም ላለባቸው እስከ 2015 በIFRS እና አነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች እስከ 2016 ዓ.ም. በIFRS for SMEs እንዲሁም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት እስከ 2016 ዓ.ም. በIPSAS መሰረት ዓመታዊ የፋይናንስ ሪፖርታቸውን አዘጋጅተው ማቅረብ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በደረጃዎቹ መሰረት ዓመታዊ የፋይናንስ ሪፖርታቸውን ማቅረብ የጀመሩ እና ትግበራቸውን እየጨረሱ ያሉ አካላት በዚሁ እንዲቀጥሉ የሚበረታቱ ሲሆን ወደትግበራ ያልገቡ ሪፖርት አቅራቢ አካላት ከወዲሁ ዝግጅት መጀመር እንዳለባቸው ዋና ዳይሬክተሯ አሳስበዋል፡፡